እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው።
“….ይህ ሕዝብ በቀስታ የሚሄደውን የሰሌሆምን ውኃ ጠልቶአልና ሪአሶንንና የሮሜልዩንም ልጅ ወዶአልና ስለዚህ እነሆ ÷ እግዚአብሔር ብርቱና ብዙ የሆነውን የወንዝ ውኃ የአሦርን ንጉሥና ክብሩን ሁሉ ያመጣባቸዋል መስኖውንም ሁሉ ሞልቶ ይመጣል ÷ በዳሩም ሁሉ ላይ ይፈስሳል እየጎረፈም ወደ ይሁዳ ይገባል እያጥለቀለቀም ያልፋል ÷ እስከ አንገትም ይደርሳል አማኑኤል ሆይ ÷ የክንፉ መዘርጋት የአገርህን ስፋት ትሞላለች።
አሕዛብ ሆይ ÷ እወቁና ደንግጡ እናንተም ምድራችሁ የራቀ ሁሉ ÷ አድምጡ ታጠቁ ደንግጡ ታጠቁ ÷ ደንግጡ ። ተመካከሩ ÷ ምክራችሁም ይፈታል ÷ ቃሉን ተናገሩ ÷ ቃሉም አይጸናም ። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነውና ። ”
(ኢሳ 8 ÷ 6-10 ) ያንብቡ።
በዚህ ላይ ኢሳያስ በሚናገረው የእግዚአብሔርን የጥበቃውን ኃይል ማየት የተሳነውን የይሁዳን ሕዝብ ያሳያል። የሚገርመው በጊዜው ይህ ሕዝብ ከጠባቂው አምላኩ ይልቅ በረአሶንና በሮሜልዩ ልጅ ደስታውን አድርጎ ነበር ። እነዚህ ሰዎች ደግሞ ወገኖች ሳይሆኑ ጠላቶች ስለሆኑ የይሁዳን ንጉስና ይሁዳን ሊወሩ የአሶር ንጉስ ሰራዊቶች ከኢየሩሳሌም በሰተቀር ሙሉ ይሁዳን እንደሚያጥለቀለቋት ነው ። የሚገርመው ግን አማኑኤል የተዋጠ ከሚመስለው ሕዝብ ጋር ነበር። ከዚያ በኋላ ነብዩ ምንም ቢበዙ እንኳን እናንተ አሕዛብ ፎክሩ ይላቸዋል ። ፎክሩ ግን ደንግጡ። ለጦርነት ተዘጋጁ ግን ደንግጡ ፣ ለጦርነት ተዘጋጁ ግን ደንግጡ። ይላቸዋል። የሚፎክር እንዴት ነው የሚደነግጠዉ? ለጦርነት የሚዘጋጅ ብርቱ ሰራዊት ያለው እንዴት ነው የሚደነግጥ? ምድሪቱን እንደወራጅ ወንዝ ያጥለቀለቀ እንዴት ነው የሚደነግጥ? የሚመካከሩ ብቃት ያለቸውን የጦር መሪዎች ከመሳረያ ጋ ያለው እንዴት ነው የማይሳካለት? በዕቅድና በፕላን የተነደፈ መዋቅር ያለውስ እንዴት ነው ንድፉ ፣የወጣው እቅዱ የማይጸናው ? ብዙ ጥያቄዎችን ልናነሳና ልናወጣ ልናወርድ እንችላለን። በዚህ ላይ ግን ለአሶር ንጉሥ ያልበራለት ሰራዊቱም ያልጠረጠረው ነገር ቢኖር ምንም እንኳን ይሁዳ ቢያጠፋ መጥፋቱ ግድ የሚለው ጠባቂ እና እረኛ የይሁዳ ጉዳይ የሚመለከተው ሁነኛ ንጉሥ ከንጉሥም ንጉሥ የነገሥታት ንጉሥ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ዳኛውና ጠበቃው ሕግ ሰጪውም የሆነ ከእርሱ ጋር እንደሆነ ነው። እረኛ እንደሌለው እንደተበተነ በግ ቢመስልም ይሁዳ በሚጠብቀው በአምላኩ ያልተጣለ ሕዝብ መሆኑን አልተገነዘበም ነበር።
ሌላው የሚገርመው በጠላት ዘንድ ማስተዋል የሚባል ነገር የለም እንጅ የእስራኤል ጠባቂ እንደማይተኛና እንደማያንቀላፋ ዳዊት በዝማሬ ተቀኝቶት ነበር። የፍልስጤም ዋነኛ በትጥቅ የተሞላ ክንደ ብርቱ እንደተምዘግዛጊ የጦር መሳሪያ በራሱ ተምዘግዝጎ የሚውጥ የሚመስል ግዙፍ የባዕዳን ጀግና ትንሹን ብላቴና በንቀት ሲዝትበት በአንዲት ጠጠር ደፋ ብሎ እንዲቀር ያደረገውን የእግዚአብሔርን ገናናነት እና ዝና ማስታወስ አልቻሉም።
ዛሬም ቢሆን ጠላቶቻችን ከእኛ ይልቅ ሰነፎች ናቸው። በጠላት ዛቻ የፈራህ ልብህም የደነገጠብህ ወገኔ ከሆነብህ ይልቅ ከአንተ ጋር ያለውን እግዚአብሔርን አስብ። ጠባቂህ እሚረታ እንጅ የሚረታ አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስን አንደ ሰው አትገምተው ሁሉን የሚረታ አምላክ ነውና።
በይሁዳ ዘንድ ሁሉ የጠፋ ሲመስል እግዚአብሔር ግን ከእነሱ ጋር ነበረ። ጠላቶቻቸውንም አሽነፈ። ሃሌ ሉያ! ዛሬም የአንተን / የአንችን ጠላት አማኑኤል በአብሮነቱ ያሽንፈዋልና በርቱ እንበርታ። እግዚአብሔር ይመስገን። እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው እና ድሉ የእኛ ነው ። አሜን!!!